የወላይታ ሶዶ ከተማ ቃለሕይወት አጥቢያዎች ኅብረት የልጆች ፌስቲቫል ሳምንትን በልዩ ልዩ መርሃ-ግብሮች አጠቃለለ።
ወላይታ ሶዶ፤ ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም
በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የወላይታ ቀጠና ቃለሕይወት ጽሕፈት ቤት ምክትል ፀሐፊ መጋቢ ያስን ያይና፣ ልጆች በሥነ-ምግባርና በበጎ ባሕርይ ታንጸው እንዲያድጉ ከማድረግ አኳያ የቤተ-እምነቶች ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁሉም አካላት በልጆች ሁለንተናዊ ስብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ቃለሕይወት አብያተ-ክርስቲያናት ኅብረት ፀሐፊ መጋቢ ኤልያስ መና በበኩላቸው፣ ልጆች ሥነ-ምግባር ያላቸው እና ጤናማ ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ ኅብረቱ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሥነ-ምግባር የታነጹ ታዳጊዎች ከአካባቢያቸው አልፈው ለሀገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ ለልጆች አገልግሎት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም መጋቢ ኤልያስ አክለው ገልጸዋል።
ልጆች በአእምሯቸው፣ በአካላቸውና በአስተሳሰባቸው የበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ በየአጥቢያዎቹ ልዩ የልጆች አገልግሎት መሪዎች ተመድበው እየሠሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማው የልጆች አገልግሎት አስተባባሪ ወንጌላዊ ታሪኩ ሰማያት ናቸው።
በዚህ በወላይታ ሶዶ ሁለገብ ስታዲየም በተካሄደው የፌስቲቫል ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ላይ በርካታ ሳቢ ተግባራት ተከናውነዋል።
ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ወንዶች የተሳተፉበት የእግር ኳስ ውድድር እና በሕክምና ተቋማት በደም እጥረት ለሚቸገሩ ወገኖች ሕይወት ማዳን የሚችል የደም ልገሳ መርሃ- ግብሮች ተካሂደዋል።
በተጠናቀቀው የ2018 የትምህርት ዘመን ከአንደኛ እስከ 11ኛ ክፍል ባሉት ክፍሎች ከአማካይ 96 በመቶ በላይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ታዳጊ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
Share This Article