WKHC

ወልድ ያለው ሕይወት አለው

99+ Years of Faith, Service & Community
▤ News ✉ Contact Us
WOLAITA KETANA KALE HEYWET
CHURCH OFFICE
Founded in Faith. Rooted in Tradition. Committed to Tomorrow.
Home About Us News Hall & Venue Media Resources Dist. Union Contact Us ♥ Donate Now
Story ✝

እማማ ባሎቴ ይባላሉ

▣ October 2, 2026
♧ Story
♙ By System
እማማ ባሎቴ ይባላሉ
አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። — የሐዋርያት ሥራ 16:14 (አማርኛ 1954)

እማማ ባሎቴ ይባላሉ፤ ከባለቤታቸው ለወንጌል ከተሰው ወንጌል አርበኛ ኦሞጨ ኡኩለ ጋር ወንጌልን ይዞ ከወላይታ ወደ ጎፋ የሄዱ የመጀመሪያ ሴት ወንጌላዊት ናቸው ።

በወላይትኛ ማንበብ እና መፃፍ ከተማሩት ከመጀመሪያዎቹ ልጃገረዶች ውስጥ አንዷ ባሎቴ ነበረች ጌታን ያወቀችው በጣሊያን ወረራ ዘመን ነበር። በምትሠራው ሥራ ሁሉ በጣም ቀልጣፋ ከመሆኗም በላይ በመዳን ያገኘችውን አዲስ ደስታና ሰላምን ለሌሎች ሴቶች ለማሳወቅና ለመመስከር በጣም ትጥራለች። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ሰልማ በርግስተን የሴቶችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖችን ለማስተባበር በየቤተ ክርስቲያኑ በምትዘዋወርበት ጊዜ አብረዋት ከሚዘዋወሩት አምስት ወይም ስድስት ሴቶች ውስጥ አንደኛዋ ባሎቴ ነበረች።

በአካባቢያዋ ባለ ቤተ ክርስቲያን የሚያመልክ ኦሞጬ የተባለ ወጣት ባሎቴን ወደዳት። ኦሞጬ ልጅ ሆኖ ከብት ሲጠብቅ አንድ ቀን ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ስለ መጣበት ራሱን ለመከላከል መሬት ለመሬት እየተንፏቀቀ ወደ አንድ ትንሽ ጉድጓድ ሲጠጋ ሳያየው አንድ ነብር የሚመስል አውሬ በቁጣ መጥቶ ጉንጩን ቧጨረው። በኋላም ቁስሉ ሲድን ከቀኝ ዓይኑ በታች ጠባሳ ሆኖ ቀረ። እርሱ ረጋ ያለና ዝምተኛ ልጅ ሲሆን ባሎቴ ግን ንቁ ነበረች። አስፈላጊዎቹ ስምምነቶች ከተደረሱ በኋላ ሁለቱ ተጋቡ። ኦሞጬም በወላይታ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ወንጌል መስበክ ጀመረ። የመጀመሪያ ልጃቸው ሴት ስትሆን አካባቢው ካሉ ልጆች የበለጠ ቆንጆና ተወዳጅ ነበረች። ስሟ ፔርሴ ይባል ነበር፥ ባሎቴና ፔርሴ መቼም አይለያዩም ነበር። ባሎቴ ከልጅዋ ጋር ስትነጋገር የምትለውን ሁሉ ልጅዋ የምትረዳ ይመስል ነበር። ባሎቴ ስለችግሯዋም ሆነ ስለደስታዋ ታወራላታለች። ባሎቴ ጥጡን እንዝርቱንና የማስታወሻ ደብተሯን የምትይዝበት በላዩ ላይ በክር ጥልፍ ወይም በእጅ ስፌት «ባሎቴ» ተብሎ ስሟ የተፃፈበት ከጥጥ ጨርቅ የተሠራ ከረጢት መሰል ቦርሣ ነበራት። ፔርሴም እንዲሁ ለሦስት ዓመት ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የምትይዝበትና በላዩ ስሟ የተፃፈበት ተመሳሳይ ቦርሣ ነበራት። ባሎቴና ፔርሲ አይለያዩም፥ ባሎቴ በሄደችበት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቦታዎችም ጭምር ፔርሴም አብራት ትገኝ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ፔርሴ ታመመች።

ባሎቴ እርጉዝ ስለነበረችና ከዚህም የተነሣ አቅም አጥታ ስለነበር ሆስፒታል ልትወሰዳት አልቻለችም። ኦሞጬም ለስብከት ርቆ ሄዷል። ዘመዶችና ጎረቤቶች ተሸክመው ሶዶ ወደ ሚሲዮኑ ሆስፒታል ቢያደርሷትም ምንም ሊደረግላት አልተቻለምና ሞተች። «በጣም የምትወዳትን የትንሿን ፔርሴ ሞት ባሎቴ እንዴት ትቀበለዋለች?» የሚለው በሁሉም ሰው አእምሮ የሚጉላላ ጥያቄ ነበር። ወደ ሆስፒታል ተሸክመው የወሰዷት ዘመዶች አስከሬን በሸማ ጠቅልለው በመሸከም ወደ ባሎቴ ተመለሱ። ከሆስፒታሉ የባሎቴ ቤት የሁለት ሰዓት ጉዞ ነበር። በነጋታው ሰልማ በርግስተን ይህንን መንገድ ተከትላ ወደ ባሎቴ ቤት ስትሄድ ምን ብላ እንደምታጽናናት እያሰበች እግዚአብሔር ከቃሉ የምትለውን እንዲሰጣት ጠየቀችው። ወደ ባሎቴ ቤት የሚያስገባውን እግር መንገድ ይዛ ስትሄድ ባሎቴ በበር ቆማ አየቻት፥ ቀርባም ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ተያይዘው ወደ ቤት ገቡ። ሚሲዮናዊቷ የማጽናኛ ቃል ከመጀመርዋ በፊት ባሎቴ « ያቺ ትንሿ ልጄ ከጌታ ጋር መኖሯ አያስደንቅምን? ባለፈው ሳምንት እዚህ ከኔ ጋር የነበረች ዛሬ ግን ከጌታ ጋር መሆኗ አያስደንቅምን? ብዙ ተወዳጅ የሆኑ ትናንሽ ልጆች እያሉ ጌታ የኔን መምረጡ! አያስደንቅምን?»እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በቤቱ እንድትኖር ልጅዋን መርጦ ስለወሰዳት እንዳከበራት ስለቆጠረች ከፍተኛ ደስታና አድናቆት አደረባት እንጂ ምንም ሐዘን አልተሰማትም። የልጇን መሄድ እንደድል ስለቆጠረች በመመረር አላለቀሰችም።

ኦሞጬ የፔርሲን መታመም ሰምቶ ሆስፒታል በተወሰደችበት ዕለት ማታ ወደ ቤቱ ጉዞ ከጀመረ በኋላ ልክ የፔርሴ አስከሬን ከሆስፒታል ወደ ቤት ተወስዶ ለቀብር ሲዘጋጅ ደረሰ። ከፔርሴ ሞት በኋላ ደስታ ተወለደ። ደስታ በጣም ዝምተኛ ከመሆኑም በላይ ንቁ ስላልሆነ ከፔርሴ የተለየ ነበር። ባሎቴ እንደ ፔርሴ ሁሉ በጣም ትወደውና ትንከባከበው ነበር። በዚህን ጊዜ ባሎቴና ባለቤቷ በስተደቡብ ምዕራብ ሁለት ሣምንት ያህል የእግር ጉዞ ርቆ በሚገኝ በጎፋ ወንጌል እንዲሰብኩ እግዚአብሔር እየጠራቸው እንደሆነ አወቁ። ኦሞጬ ቤት ሊሠራ ሚችልበትን ቦታ ለመፈለግና ለመምረጥ አስቀድሞ ወደ ጎፋ ሄደ። በዚያም ወንጌል ያልደረሰበትን ጎሣ በማግኘት በአካባቢው ባለ ኮረብታ ጎን ጥሩ መሬት መርጦ ቤት ከሠራና አትክልት ከተከለ በኋላ ባሎቴንና ደስታን ለመውሰድ ወደ ወላይታ ተመለሰ።

የተመለሰውም ዓመታዊው ኮንፈረንስ ሊከፈት ጥቂት ቀናት ሲቀረው ነበር። ኮንፍራንሱ አልፎ ጎፋ የሚሄዱበት ጊዜ ደረሰ። ሌላም ወንጌላዊ ከሚስቱ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ጎፋ የሚሄድ በመሆኑ የሚያስፈልጋቸውን እህል በራሳቸው ከመሸከም ይልቅ በአህያ ጭነው እንደሚጓዙ ሁለቱ ቤተሰቦች ተስማሙ። ስንቃቸውን ሰብስበው በአንድ ትንሽ አህያ ጫኑ። ባሎቴ በአንድ እጇ በትንሽ ማሰሮ ወተት በሌላ እጇ ደግሞ በቅል የተሞላ የስንዴ ዱቄት ከመያዟም በላይ ደስታን በጀርባዋ አዝላለች። ኦሞጬ አህያውያንና ላሟን ይነዳ ነበር። .
እንግዲህ ኦሞጬና ባሎቴ ሁሉንም ትተው ቤታቸውንም ለቀው ወጡ።

ጥሩ ጎረቤቶችን እንዲሁም ደግሞ ሁሉ የሚገኝበትና የሚገዛበት ገበያ በቅርብ ያለበትን አካባቢ ወደኋላ ትተው ጉዞ ጀመሩ። ካላቸውም ሁሉ ካንዲት ላም በስተቀር ቤታቸውን፥ የእርሻ መሣሪያዎቻቸውን፥ የውሃ እንስራዎችንና የሸክላ ምጣዳቸውን አልያዙም። እነዚህ በገንዘብ ሲተመኑ ብዙ ላይሆኑ ቢችሉም ለእነሱ ግን ትልቅ መስዋዕት መክፈል ያህል ነበር። ሆኖም ወንጌልን ላልሰሙት አሰምተው ክርስቶስን ለማሳወቅ ወደ ጎፋ ለመሄድ ሲሉ ምቾቶቻቸውን በወላይታ ጥለው መሄድ በመቻላቸው ተደሰቱ።

ከባለቤታቸው ጋር ወንጌልን እየሰበኩ እያሉ ባለቤታቸው በወንጌል ምክንያት በሰው እጅ ከተገደለ በኋላ ወደ ቤት እንዲመለሱ ተጠይቆ እንብ እንደ ባለቤቴ ለወንጌል መሞትን እመርጣለሁ በማለት ወንጌልን ያስቀጠሉ ጀግና የወንጌል አርበኛ ናቸው። እንደ ደመና ስለከበቡን ወንጌል አርበኞች ክብር ለጌታ ይሁን!

ምንጭ : Fire on the Mountains: by Raymond J. Davis in 1966 GC (page 196)
Share This Article